በአማራ ክልል የመጀመሪያው የኢንፍሎዌንዛ መመርመሪያ ቤተሙከራ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ የመጀመሪያ የሆነውን የኢንፍሎዌንዛ ቫይረስ ቤተሙከራ ምርመራ አገልግሎትን ዛሬ አስጀመረ።
የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ከኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የጤና ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያስጀመረው ቤተሙከራ የመተንፈሻ አካላትን ለሚያጠቁ በሽታዎች የምርመራ አገልግሎት በመስጠት የሕሙማንን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ነው የተባለው።
ቤተሙከራው የሚያስፈልጉትን ግብዓት በማሟላት ለሥራ ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በሰጡት ማብራሪያ÷ ለኅብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የኢትዮጵያ የጤና አብያተ ሙከራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
የኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የጤና ፕሮግራም በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ለተዘረፉና ለወደሙ ዘጠኝ ሆስፒታሎች መልሶ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉንም አውስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው÷ በጤናው ዘርፍ ለኅብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በሽታዎችን መመርመርና ማወቅ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ትብብር ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአራት ክልሎች የኢንፍሎዌንዛ መመርመሪያ ቤተ ሙከራ ሥራ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን÷ወደ ሌሎች ክልሎችም የማስፋፋት ጥረቱ ይቀጥላል ተብሏል፡፡
የኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የጤና ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ወንዶሰን ገብረየስ በበኩላቸው፥ በአማራ ክልል የኢንፍሎዌንዛና ሌሎች ተዛማች በሽታዎችን ለመከላከል እየሠሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መጋለጻቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡