በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቡ ለሰላምና ለልማት መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ህብረተሰቡ ለሰላምና ለልማት መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የክልሉን እና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ የመሪነት ሚናቸውን ለተወጡ አመራሮች የእውቅና መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ መተከልና ካማሽ ዞኖች የነበረው የጸጥታ ችግር በዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል እንዲሁም የንብረት ውድመት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡
ችግሮችን ተቋቁሞ የክልሉን ሰላም ለመመለስ በተደረገው ጥረት÷ የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት እንዲሁም አመራሩ ካደረገው ርብርብ በተጨማሪ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ያለውን አንፃራዊ ሰላም በማስቀጠል፣ ከግጭት ለማትረፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመታገል እና ልማትን በማፋጠን አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡
ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሰላምና ለልማት መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መርሐ ግብሩን የክልሉ ንግድ ማህበረሰብ “ክብር ለሚገባው ክብር እንሰጣለን” በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!