Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ የክምችት መጠንን የሚያሳውቅ የመጀመሪያው ጥናታዊ ሰነድ ይፋ ሆነ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ የድፍድፍ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መጠን የሚያሳውቅ እና እንዴት ማውጣት እንደሚቻል የሚጠቁም የመጀመሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ይፋ ሆኗል።

ጥናቱ ከዚህ በፊት ሲደረጉ ከነበሩት ጥናቶች በተለየ መልኩ ለአራት ወራት ሲካሄድ መቆየቱን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።

ጥናቱን ያካሄደው “ኒዘርላንድ ሲዌል ኤንድ አሶሼየትስ” የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ መሆኑም ተገልጿል።

በሀገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ መጠን እና የኢኮኖሚ አዋጭነት የያዘ ሰነድ ዛሬ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ርክክብ ተደርጓል።

በሰነዱ ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ ኢንጂነር ታከለ ኡማ÷ ከዚህ ቀደም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳለ ብቻ እንጂ በምን ያህል መጠን አለ የሚለው የሚታወቅ ባለመሆኑ ሃብቶቹ በተለያዩ ኩባንያዎች እንዲመዘበሩ ሲያደርጋቸው መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም ይህ ቴክኖሎጂ ይህንን ችግር የሚቀርፍ እና ተጠያቂነትን የሚፈጥር በመሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

ዛሬ የተቀበልነው ሰነድ የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ የማልማት ሀገራዊ እቅዳችንን አንድ እርምጃ ያራመደና በትልቁ የመንግስት ቁርጠኝነት የታየበት ስራ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ይህ ሰነድ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ መጠንና የኢኮኖሚ አዋጭነት የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ነው፤ይህንን ሰርተፊኬት ይዘን በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ፣የፋይናንስ እና በዚህ ኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው ኩባንያዎች መጋበዝ ይቻለናል፤ የመንግስትን የመደራደሪያ አቅምንም ያጎለበታል ነው ያሉት፡፡

የተዛባ መረጃ ይዘው ሀብታችንን እስረኛ እያደረጉ ላሉ ኩባያዎችም ጥሩ ማንቂያ ይሆናል ብዬ አምናለው ያሉት ሚኒስትሩ በስራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፥ ወደ ተግባር የመቀየሩ ጉዳይም እንደ አሰራራችን ፍጥነት የሚወሰን ይሆናል ብለዋል፡፡

በምንይችል አዘዘው እና አመለወርቅ ደምሰው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.