በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሰላም ዙሪያ ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩ አረጋገጡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን “ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ጦርነት እስኪያበቃና የሀገር ሉዓላዊነት እስከሚከበር ከመንግስት ጋር በመሆን የበኩላችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን” ሲሉ አረጋገጡ፡፡
በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪው ሕወሃት ቡድንን በማውገዝ ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
ባወጡት የአቋም መግለጫ፥ ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ጦርነት በመጀመር በሀገሪቱ ላይ ለደረሰው የሰው እልቂትና የንብረት መውደም እንዲሁም በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመደቀን ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም ግብዣ ወደ ጎን በማድረግ በህዝቦችና በሀገር ህልውና ላይ ዳግመኛ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል፡፡
በዚህም ጦርነቱ እንዲቀጥልና ሀገሪቱ በተለያየ መንገድ እንድትዳከም ከጀርባ ሆነው የሚወጉ ሁሉ የኢትዮጵያ ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነትን ከሚያደፈርስ ተግባር ሁሉ እጃቸውን እንዲያነሱ አሳስበዋል፡፡
የአመለካከት ልዩነት ሳይበግራቸውም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በመሣተፍ ሀገሪቱ ሰላም እንድትሆን፣ ጦርነት እስኪያበቃና የሀገር ሉዓላዊነት ሙሉ ለሙሉ እስከሚከበር ከመንግስት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸው አረጋግጠዋል፡፡