የአዲስ አበባ እና የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራመዋል።
የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እና የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ፑሌንግ ላንካካቡላ ተፈራርመውታል፡፡
ስምምነቱ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በጥናትና ምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በሰው ሃብት ልማትና ተቋም ግንባታ በልምድ ልውውጥና ሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሥራት እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት የፈጸሙት ስምምነት የአፍሪካውያንን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የሚጋራቸው ተሞክሮዎች እንዳሉት ጠቅሰው÷ ዩኒቨርሲቲዎቹ በትብብር ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር በማድረግ የዜጎችን ሕይወት መቀየር የሚያስችል አህጉራዊ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ፑሌንግ ላንካካቡላ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ በቴክኖሎጂ፣ በጥናትና ምርምር፣ በትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት እንደሚያግዝ ገመግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።