ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ደጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን በመወከል በደቡብ ሱዳን የተወሐደ ሠራዊት የምርቃ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከጀምሩ ያልተቆጠበ ጥረት ስታደርግ መቆይቷን አውስተዋል።
በአገሪቱ ቀደም ሲል ሲፋለሙ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ላይ ሠራዊቶቻቸውን በማዋሐድ አንድ አገራዊ ጦር መገንባት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
እ.ኤ.ኤ በ2018 በአዲስ አበባ የሰላም ስምምነቱን የፈረሙ ኃይሎች አሁን በጀመሩት መልኩ ቁርጠኝነታቸውን በማጠናከር ቀሪ የስምምነቱን ክፍሎች ሙለ ለሙሉ እንደሚተገብሩ ያላቸውንም እምነት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ለሂደቱ መሳካት ስታደረግ የቆየቸውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የዩጋንዳና የሱዳን መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ሌሎች የአካባቢው አገራት፣ የክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ተወካዮች መገኘታቸውንም ከጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መተጃ ያመላክታል። ።