በመዲናዋና አካባቢዋ በ2014 ዓ.ም በተከሰቱ አደጋዎች የ115 ሰዎች ሕይወት አልፏል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በ2014 ዓ.ም በተከሰቱ 511 ድንገተኛ አደጋዎች የ115 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከደረሱት አደጋዎች መካከል 362 የእሳት ሲሆኑ 149 የጎርፍ፣ የኮንስትራክሽን፣ የወንዝና የኩሬ አደጋዎች ናቸው፡፡
በደረሱት አደጋዎች ምክንያትም የ115 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ200 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ሕይወታቸው ካለፈው 115 ሰዎች መካከል 14ቱ በእሳት አደጋ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው÷ ቀሪዎቹ 101 ሰዎች ደግሞ በተለያየ ድንገተኛ አደጋ ነው ሕይወታቸው ያለፈው ብለዋል፡፡
በደረሱት አደጋዎች ምክንያት 577 ሚሊየን 780 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ያሉት አቶ ንጋቱ÷ በአንጻሩ በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ርብርብ 39 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከደረሱት አደጋዎች መካከል የ137 አደጋዎች መንስኤ መታወቁን ጠቁመው÷ 63 በኤሌክትሪክ ምክንያት የደረሱ አደጋዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ አብዛኛዎቹ አደጋዎች ያጋጠሙት በጥንቃቄ ጉድለት መሆኑንም ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡
ሰሞኑንም የበዓል ወቅት እንደመሆኑ ከፍተኛ የኃይል አጠቃቀም እንደሚኖር ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ ከምግብ ማብሰል ጋር ተያይዘው ለሚሠሩ ሥራዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው