በመዲናዋ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 188 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ መጋቢት 8፣ 201 2(ኤፍ ቢ ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 188 ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በመዲናዋ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ በማድረግና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር አጋጣሚውን ሲጠቀሙ ተገኝተዋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደገለጹት በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በሸቀጦች ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚቆጣጠር ግብረኃይል ተቋቁሟል።
ግብረ ኃይሉ ትናንት ባካሄደው ፍተሻም 188 የንግድ ድርጅቶች በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ያለአግባብ ለመበልፀግ ሲሰሩ መገኝታቸውን አስታውቋል።
ይህ ግብረኃይል ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ከመከታተል፣ ከመቆጣጠርና አጥፍተው ሲገኙ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ ባሻግር አቅርቦት እንዲሻሻል ይሰራል ነው ያሉት።
በተደረገው ፍተሻ በተለይ በነጭ ሽንኩርት፣ ጤፍ፣ ሎሚ፣ በርበሬና ዝንጅብል ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።
ግብረኃይሉ ቫይረሱን ለመከላከል በሚያስፈልጉ የፊት ማስክና ሌሎች ኬሚካሎች ላይ እየተደረገ ያለውን የዋጋ ጭማሪ እየተከታተለ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ከዋጋ ጭማሪው ባሻገር የሸማቹን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ጥራት የሌለው ምርት ለገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎችም ተገኝተዋል ነው ያሉት አቶ አብዱልፈታህ።
በአንዳንድ የመድሃኒት መሸጫ መደብሮች በአስፈላጊ ቁሳቁሶች ላይ ዋጋ ከመጨመር ባሻገር ተጠቃሚው የማይፈልገውን ምርት እንዲወስድ የማስገድድ አዝማሚያም ታይቷል ብለዋል።
በሽታውን መከላከል የሚቻለው የሚመለከተው አካል በሚገልፀው መንገድ ብቻ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ባልተረጋገጡ መረጃዎች በመደናገር ገንዘቡን ያለአግባብ ማውጣት እንደሌለበትም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኅብረተሰቡ በሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው በስልክ ቁጥር 0118545815 እና 0118 548397 ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።