አሸባሪውን ህወሓት የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን እሁድ በዋሺንግተን ዲሲ ይካሄዳል፡፡
ኋይት ሐውስ ፊት ለፊት የሚከናወነው ሰልፍ÷ የተለያዩ አላማዎችን ያነገበ መሆኑን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ጣሰው መላከህይወት ገልጸዋል።
“አሜሪካ የሽብር ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት በይፋ በማውገዝና ለአፍራሽ ድርጊቱ ተጠያቂ ማድረግ አለባት፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም ይኖርባታል” የሚሉ መፈክሮችን እንደሚያሰሙ ጠቅሰዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዳግም ልታጤነው እንደሚገባ የሚያሳስቡ መልዕክቶችም እንደሚተላለፉ ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያን የሚደግፍ የትዊተር ዘመቻም ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን አቶ ጣሰው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም አሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተቋቋሙ የሲቪክ ተቋማትና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች በፈረንጆቹ 2022 በአሜሪካ በሚካሄደው የአጋማሽ ዓመት ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ስራ ላይ የሚሳተፉ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በድምጽ የመቅጣት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፉበታል ነው የተባለው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!