Fana: At a Speed of Life!

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የነበረ ተጠርጣሪ ከ20 የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ ተያዘ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የነበረ ተጠርጣሪ ከ20 ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

 

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ጥቆማ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ህገወጥ የጦር መሳሪያ በባጃጅ ተሽከርካሪ በማጓጓዝ ወደ መኖሪያ ቤቱ ለማስገባት ሲሞክር ተደርሶበት እንደሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ሙሉጌታ ሩት ገልጸዋል፡፡

 

ከተጠርጣሪው ጋር 11 ባለሰደፍ እና ዘጠኝ ታጣፊ በድምሩ 20 ክላሽንኮቭ መያዙን ጠቁመው በተጨማሪ 34 የክላሽንኮቭ ካርታና የተለያዩ የባንክ ደብተሮች፤ ዶክመንቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

 

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ተጨማሪ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ኅብረተሰቡ ተጠርጣሪውን ከነጦር መሳሪዎቹ ለመቆጣጠር ያደረገውን ትብብር ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ አስተዳደር  የከተማው ጸጥታ ኃይል በመኝታ ቤቶች ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ህገ ወጥ ተተኳሽ ጥይትና ቦንብ መያዙ ተገልጿል፡፡

 

በዚህም ነዋሪነታቸው ወግዲ ወረዳ የሆኑ ሁለት ግለሰቦች  ከተሁለደሬ ወረዳ ሰግለን ቀበሌ ገዝተው ወደ ወግዲ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሊያጓጉዙ ባረፉበት መኝታ ክፍል ውስጥ 477 የክላሽ ጥይት፣ 173 የብሬን ጥይት፣ 7 የክላሽ ካዝና፣ 8 ኤፍ ዋን ቦንብና ከ16 ሺህ 150 ጥሬ ብር ጋር በቁጥጥር  ስር ውለዋል፡፡

 

አሰፈላጊው ምርመራም እየተጣራባቸው መሆኑን የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ም/ ኮማንደር መሀመድ አሊ መናገራቸውን ከአማራ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.