Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በ699 ጤና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ባካሄደው የደረጃ ልየታ 699 ጤና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አምደየሱስ አድነው፥ በመዲናዋ በጤና ቁጥጥር ዘርፍ ያለውን ብልሹ አሰራር በመለየት እና የእርምት እርምጃ በመውሰድ ለህብረተሰቡ ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎትና የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ከማዕል እስከ ወረዳ ብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት ከሀገር አቀፍ መስፈርት አንፃር ተቋማትን እንደ የደረጃቸው ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አጠቃላይ 2 ሺህ 537 ተቋማት ላይ የደረጃ ልየታ የተደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ከ75 በላይ ያስመዘገቡ እና በአረንጓዴ ደረጃ የተቀመጡ 1 ሺህ 586 ተቋማት ብቻ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የአሰራር ችግር ከታየባቸው ውስጥ ማስጠንቃቂያ 84፣ የሶስት ወር ጊዜ ማስጠንቃቂያ 473፣ ውስን አገልግሎት የታገደባቸው 34፣ ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የታገዱ 108 በድምሩ 699 ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡
አስተኝቶ ማከሚያ ክፍል፣ መድኃኒት ቤት ያለመኖር፣ የፍሪጅ ቅዝቃዜን ሁኔታ በመመዝገብ አለመከታተል እና ማቀዝቀዣ ውስጥ ከመድሃኒት ጋር ምግብ ማስቀመጥ፣ መድሃኒት የተገዛበት ደረሰኝና የድንገተኛ መድሃኒቶች መመዝገቢያ መዝገብ አለመኖር የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የአገልግሎት ጊዜ ያለፈበት መድሃኒት መያዝ፣ ባለሙያ ያልሆነ ሰው ሲሰራ መገኘትና ከሙያ ዘርፍ ውጪ ሌላ ሰው መድቦ ማሰራት ከስነ ህንፃ፣ ከሙያዊ ትግበራ፣ ከግብዓትና ከባለሙያ አንፃር የተገኙ ዋና ዋና ጉድለቶች መሆናቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡ በማንኛውም አገልግሎት ቅሬታ ወይም ጥርጣሬ በሚያስተውልበት ጊዜ በባለስልጣኑ ነጻ የስልክ መስመር 8864 ላይ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.