Fana: At a Speed of Life!

የሙያተኝነት መስፈርትን ሳያሟላ የተዘጋጀውን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት እንዲቃወሙ ኢትዮጵያ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ያቀረበውን ከደረጃ በታች የወረደ ሪፖርት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት እንዲቃወሙ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች።

በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፥ የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰሜኑን ግጭት ተከትሎ ሊኖሩ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን በጋራ ምርመራ በማድረግ ሪፖርት ማውጣታቸውን አስታውሷል።

የኢፌዴሪ መንግስትም የጋራ ምርመራ ሪፖርቱ ያስቀመጣቸውን ምክረ ሃሳቦች በመቀበል የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል በማቋቋም ጭምር ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃ መወስዱንም ነው ያመለከተው።

መንግስት በቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረትም ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መስራቱን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳቱን ነው ያስታወሰው።

በተጨማሪም ላልተገደበ ጊዜ ግጭትን በማቆም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል በተሳለጠ ሁኔታ እንዲቀርብ ማድረጉን እና በክልሉ ተቋርጠው የነበሩትን የመሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደነበረም አመልክቷል።

በዚህ ሁሉ ጥረት መሃል ቀድሞውኑ የፖለቲካ አጀንዳ አንግቦ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች በኢትዮጵያ፥ ከተሰጠው ሃላፊነት በመውጣት የተመድን የአጠናን ስነ ዘዴ እና ሙያተኝነትን ባልተከተለ መልኩ አደረኩት ያለውን ምርመራ ሪፖርት ማዘጋጀቱን ገልጿል።

ይህ ምርመራ ቀደም ሲል የተካሄደው የጋራ ምርመራ ያልሸፈናቸውን ቦታዎች እና ጊዜ ብቻ ሸፍኖ መካሄድ ቢገባውም ከዚያ ባፈነገጠ መልኩ ለፖለቲካ ግቡ የሚያመቸውን ሁነትና ጊዜ ብቻ ለይቶ መጠናቱን ጠቁሟል።

እንደዚሁም በመሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ በቦታው ተገኝቶ እንዲመረምር የቀረበለትን እድል ከመጠቀም ይልቅም በርቀት ምርመራ ለማድረግ በመሞከር ከሙያተኝነት ያፈነገጠ ድርጊት መፈፀሙ በመግለጫው ተጠቅሷል።

ይህ በብዙ መስፈርቶች ያልተሟላ ምርመራ ውጤት በሪፖርትነት ሊወሰድ እንደማይችል አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግን የፖለቲካ ጫናን ለመቀጠል ከመፈለግ የተዘጋጀው ሪፖርቱ፥ በሀገሪቱ ውስጥ ውጥረትን ከማባበስ እና የሰላም ጥረቶችን ከማስተጓጎል የዘለለ ሌላ ሚና አይኖረውም ብሏል።
ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ በተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተካሄደው የጋራ ምርመራ ላይ ምንም ዓይነት እሴት እንዳልጨመረ ይልቁንም የጋራ ምርመራ ውጤትን ለማሳነስ መሞከሩን ገልጿል።

በተጨማሪም ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ መስጠቱን ጠቁሟል።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት የፈፀማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመሸፈን ሲልም ቡድኑ አሰቃቂ የሰብዓዊ ድርጊት የፈፀመባቸውን ቦታዎች እና ጊዚያቶች ሆነ ብሎ ከምርመራ ስራው እንዳስወጣም አመልክቷል።

በህወሃት የተፈፀመን የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሆነ ብሎ ማስወጣቱ አደገኛ ወንጀል መሆኑን አስታውቋል መግለጫው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሰዎችን ሊከላከል የተቋቋመ ሀይል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፥ ይህ ሀይል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ይጠብቃል ብሏል።

በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀምን ምንም ዓይነት ጥቃትንም አይታገስም ነው ያስታወቀው።

የመከላከያ ሰራዊት በጋራ ምርመራው የቀረቡ ክሶችን በሙሉ እንደመረመረ እና በወታደራዊ የፍርድ ሂደት ጉዳዮችን እንደተመለከተ አስረድቷል።

በግለሰቦች ላይ የሚነሳ ምንም ዓይነት ክስ የዚህን ሰራዊት ስም ለማጉደፍ መሰረት ሊሆን አይችልም ብሏል።

በመሆኑም የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባላት ከደረጃ በታች የወረደውን ይህን ሪፖርት እንዲቃወሙ እና የኮሚሽኑን የስራ ጊዜ ለማራዘ የሚቀርብ ሀሳብን ውድቅ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.