“መቻዕል ሜራ”- የእብደት ገበያ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “መቻዕል ሜራ” (የእብደት ገበያ) የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ በዓል “ያሆዴ” ሊከበር 15 ቀናት ሲቀሩ የሚጀምር ለበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ ነው።
መቻዕል ሜራ ተብሎ የሚጠራው ገበያው በአቻ ትርጉም ለመግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም ፅንሰ ሀሳቡ ግን የእብደት ገበያ የሚል ፍቺን ይይዛል።
ይህም መጠሪያ ከግብይት ስርዓቱ ባህርይ በመነሳት የተሰጠ ስያሜመሆኑ ይነገራል፡፡
በመቻዕል ሜራ የማይሸጥና የማይለወጥ ነገር የለም፤ገበያ ተገብቶም የለም የሚል ቃል አይሰማም፤ዓመቱን ሙሉ በልዩ ሁኔታ ሲቀለብ የነበረ ሰንጋ፣ ቆጮ፣ ቅቤ፣ ማር፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም የምግብና የማስዋቢያ ቁሳቁሶች ከአፍ እስከ ገደፉ በሞላው ገበያ ውስጥ ይገኛሉ።
በመቻዕል ሜራ ገበያው የሚደራው በተለመደው ሰዓት ሳይሆን ግብይቱ ከሌሊት ይጀምራል።
አርፍዶ ወደ ሰንጋ ሸመታ የሄደ አባወራና በጠዋቱ የእብደት ገበያውን ያልተቀላቀለች ሴት እንደ ሰነፍ ስለምትቆጠር ሁሉም በተመሳሳይ ሰዓት ከገበያው ስፍራ በመድረስ ሸመታ ይጀምራሉ።
በዚህም ምክንያት የእብደት ገበያው በሚሸምቱ ሰዎች፣ ለገበያ በሚቀርቡ እንስሳት እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ይጥለቀለቃል።
የእብደት ገበያ በዓመት አንዴ የሚመጣ ገበያ እንደመሆኑ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካልገጠመ በቀር ሁሉም ሰው እንዲያመልጠው አይፈልግም።
በዚህም ምክንያት ግብይቱ በገበያው ስፍራ ብቻ አይወሰንም ፤ገበያተኛው እና ምርቱ ከገበያው አቅም በላይ ይሆናልና መንገዶችም ለግብይት እንዲውሉ ይገደዳሉ።
ጥድፍያው፣ ግርግሩ ፣የገዢና ሻጭ ትርምሱና ሁካታው ተዳምረው መቻዕል ሜራን በርግጥም የእብደት ገበያ ያስመስሉታል።
በእብደት ገበያ አባቶች ገንዘብ የለኝም ብለው ከሰንጋ ገበያው አይቀሩም፤ ያሆዴ የደስታና የመተሳሰብ በዓል ነውና በመንደራቸው ያለ የአንድ ታዋቂ ሰው ስም በመጥራትና አድራሻቸውን በመግለፅ ብቻ ያሻቸውን ሰንጋ እየጎተቱ በዱቤ መውሰድ ይችላሉ።
ክፍያውም አጣዳፊ አይደለም፤ ከታህሳስ እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ምርት ሲደርስ ክፍያውም በታማኝነት ይፈፀማል።
የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” አንዱ አካል የሆነው እና ለሰባት ቀናት የሚካሄደው መቻዕል ሜራ ተራርቆ የነበረ ወዳጅ ዘመድ የሚገናኝበት፣ ወጣት ወንዶች እና ልጃገረዶች በገበያ ሰበብ የሚተያዩበት(ከቀናቸውም የሚተጫጩበት) ገበያ ነው።
የሀዲያ ዘመን መለወጫ ያሆዴ መስከረም 14 በ”ሀዲይ ነፈራ”ይከበራል፡፡