Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት የሙያ ስነ ምግባርን የደፈጠጠ ነው – ተመራማሪ ዶ/ር ዳርእስከዳር ታዬ

 

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያወጣው ሪፖርት የሙያ ስነ ምግባርን የደፈጠጠ ነው ሲሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ ገለጹ፡፡

 

ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ ሰብዓዊ መብትን ለፖለቲካ ጥቅም ስለማዋል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

 

ስለ ሰብዓዊ መብት ግድ የማይላቸውና በራሳቸው ህግ ብቻ የሚመሩ ሀገራትን ፥ በሰብዓዊ መብት ከመክሰስ ይልቅ ወዳጅ ሆነው የተለያዩ ድጋፎች የሚያደርጉባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል።

 

እነርሱ የሚፈልጉትን አጀንዳ የማያስፈጽሙ ሀገራትን ግን በሰብዓዊ መብት ሰበብ ሲወነጅሉ ይታያሉ ለዚህ ማሳያ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት ብለዋል፡፡

 

ምዕራባውያኑ ብዙ ጊዜ በሰብዓዊ መብት እኔ አውቀላችኋለሁ በማለት ፥ በየሀገራቱ በሚከተሉት ፍላጎት ሰብዓዊ መብትን እንደመሳሪያ እንደሚጠቀሙም ነው የገለጹት፡፡

 

ሀገራትን ለማጥቃትና ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ከሚጀምሩ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ቀጥለው የሚዲያ ዘመቻ እንደሚከፍቱም ገልጸዋል፡፡

 

የመጀመሪያው የኮሚሽኑ ሪፖርት በመጠኑም ቢሆን ሙያዊ እንደነበር አስታውሰው ፥ ይህም የፈለጉትን ውጤት ባለማምጣቱ ሰሞኑን የወጣው ሪፖርትን ከዜሮ በመጀመር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየጣሩም ነው መሆኑን ያነሳሉ፡፡

 

የመጀመሪያውን ሪፖርት መነሻ ያላደረጉበትን ምክንያት ሊያነሱና ሙሉ በሙሉ ሪፖርቱን መጣላቸውን ሊያሳውቁ ይገባ እንደነበርም ነው ያነሱት ተመራማሪው ፡፡

 

ጦርነቱ በአማራና አፋር ክልል መካሄዱን በጨረፍታ ያሳየው ሪፖርቱ በአብዛኛው በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉም አንስተዋል።

 

በዚህም የኮሚሽኑ ሪፖርት የሙያ ስነ ምግባርን የደፈጠጠ ነው ያሉት ተመራማሪው ፥ እንደሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ሁሉንም ቦታ ባማከለ መልኩ ሊሰራ ይገባው እንደነበር አውስተዋል።

 

በተጨማሪም በጥናቱ የጦርነቱን መነሻ ማጥናትና ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ፥ በሪፖርቱ ይህን ማሳየት እንዳልቻሉና ፍላጎቱም እንደሌላቸው አንስተዋል፡፡

 

ምክንያቱን ሲያነሱም የጦርነቱን መነሻ፣ ጠንሳሽ፣ ዋና ተዋናይ ማነው የሚለውን ካነሱ ችግሩ የማን እንደሆነ በግልጽ ስለሚያሳይ ይህን እንደማይፈልጉትም ነው የጠቆሙት፡፡

 

በተጨማሪም ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይን አንድ የምርምር ዘዴን ብቻ በመጠቀም መስራት የጥናቱ ውጤት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይጠቅሳሉ፡፡

 

በዚህም ሰዎቹን መልምሎ የሚሰጠው ማነው የሚል ሌላ ጥያቄ እንደሚያስነሳ በመጥቀስም የተጠቀሙት የምርመራ ዘዴ በቂ እንዳልሆነም ነው ያመላከቱት፡፡

 

ይህን ማድረግ ካልቻሉም ጦርነቱ እስከሚበርድ መጠበቅ እንደነበረባቸው የገለጹት ተመራማሪው ፥ ይህም በጥድፊያ ሪፖርት አድርጎ ጫና ለማሳደር ስለፈለጉ ጥራት የሌለውና ስህተት የሆነ ሪፖርት ይፋ ማድረጋቸውን ነው የሚገልጹት፡፡

 

ሪፖርቱ የሚያነሳው የትግራይን ህዝብ ብቻ ተጎጅ በማድረግ ነው ያሉት ተመራማሪው፥ ይህም ሪፖርቱ የህወሓት ሪፖርት ነው ለማለት ያስገድዳል ብለዋል፡፡

 

ሪፖርቱ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የደረሰውን ጉዳትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የረሳ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

 

በሪፖርቱ የተጠቀሙት የምርመራ ዘዴም ምንም ማጣራት የሌለበትና በአንድ የመረጃ ምንጭ ብቻ ተመስርቶ የወጣና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ጥናት ዓላማ መሆን የነበረበትም ዳግም በኢትዮጵያ ጦርነቱ እንዳያገረሽና የተጎዱ ዜጎችን መካስ ሊሆን ይገባ እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡

 

በመሰረት አወቀ እና አመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.