የመጪው በጋ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛ በታች እንደሚሆን ይጠበቃል
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጪው የበጋ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛ በታች እንደሚሆን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ ።
ኢንስቲትዩቱ ያለፈው የክረምት ወቅት ትንበያ ግምገማና የመጪው የበጋ ወቅት የአየር ጸባይ ትንበያ ላይ የሚመክር መድረክ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት÷ የአየር ጸባይ ክስተቶች ሊያሳድሩ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን በመከታተል መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች የማድረስ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
አሁን ባለው ትንበያው መሰረትም ደቡብ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ክልል እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በአማካይ ከ200 ሚሊ ሊትር የማይበልጥ የዝናብ ስርጭት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
በዚህም የፓስፊክ ዊቂያኖስ ከመደበኛ በላይ መቀዝቀዝና የህንድ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ክፍል መሞቅ ሀገራችንን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የዝናብ ስርጭት ከመደበኛ በታች እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት።
በዚህም ሊኖር የሚችለውን ከመደበኛ በታች የሆኑ የዝናብ ሁኔታን መቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ ወሳኝ እንደሆነ መግለፃቸውን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡