የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ የሰላም ሰራዊት አባላት ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን በሰላም ለማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።
በኮሚሽኑ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ÷ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሁሉም የመዲናዋ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ የሰላም ሰራዊት አባላተን በማደራጀት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰራዊት አባላትም የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ረዳት ኮሚሽነር ፋሲካ ፋንታ አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ለገሰ በበኩላቸው ÷ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ በዓላቱን የሚመጥን የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ስኬታማ የሰላምና ደህንነት ስራን ለመስራትም የጸጥታ ኃይሉ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ዜጎችን በሚገባ በማስተናገድና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲስተዋል ጥቆማ በመስጠት የመዲናዋ ነዋሪዎች እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በጎ ፈቃደኛ የሰላም ሰራዊት አባላትም የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለመዲናዋ ሰላም ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አጠራጣሪ ነገሮችን በማክሸፍ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!