በሔክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የሩዝ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሔክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የሩዝ ዝርያዎችን አበልጽጎ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ እየሠራ መሆኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሩዝ ምርትን በቆላማ አካባቢዎች የማላመድና የማስፋት ሥራ እየሠራ መሆኑን የገለጸው ማዕከሉ÷ ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ምርጥ ዘሮችን በምርምር እያስፋፋ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በማዕከሉ የሰብል ቴክኖሎጂ አስተባባሪና የሩዝ ሰብል ተመራማሪ አሳየ ብርሃኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በረግረጋማ አካባቢዎች የሚመረተውን የሩዝ ሰብል በቆላማ አካባቢዎች የማላመድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ቆላማ የአየር ጠባይ እንዳለው ገልጸው ይህም ለሩዝ ምርት ልማት ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረጉ ጥናቶችና ሙከራዎች÷ ሩዝን በማላመድ አርሶአደሮች እስከ 8 ሺህ ሔክታር በአንድ ጊዜ ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡
በምርምር ማዕከሉ የበለፀጉና ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ እየተዋወቁ ያሉት የሩዝ ዝርያዎችም÷ በሔክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ከሰሊጥና ጥጥ እንዲሁም አኩሪ አተር በተጨማሪ የሩዝ ምርትን እያለማ እንዲጠቀም በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሙሉጌታ ደሴ