Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ሚኒስቴር ተማሪዎችን ለማሰልጠን ከስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር በመሬት አስተዳደር ዘርፍ በአጭር፣ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎችን ለማሰልጠን ከስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የስምምነት ፊርማ ተፈራርሟል።

የመሬት አስተዳደር ዘርፉን ለመምራትም በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ከ138 ሺህ በላይ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የተፈረመው ስምምነት በዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ስምምነቱ ከባህር ዳር፣ አምቦ፣ ደብረማርቆስ፣ ዲላ፣ ሐዋሳ እንዲሁም ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተፈረመ ሲሆን ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚሰራውን ስራ የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሰረት ሚኒስቴሩ 2 ሺህ 400 ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ ስልጠና፣ 370 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም 40 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር በመሬት አስተዳደር ትምህርት ዘርፍ የሚያሰለጥን ይሆናል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፥ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ የተሻሻለ የእርሻ መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

የመሬት አስተዳደር ስርዓት አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን በአግባቡ ተጠቅሞ እንዲያለማ የሚያስችል እና የይዞታ ባለቤትነትን በህጉ መሰረት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.