Fana: At a Speed of Life!

“ብቃት” በተሰኘ ፕሮጀክት እስካሁን ምንም አይነት ሥራ ያልጀመሩ ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ እየሠራሁ ነው – የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ብቃት” በተሰኘ ፕሮጀክት እስካሁን ምንም አይነት ሥራ ያልጀመሩ ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዛሬ በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ፣ ሐዋሳ ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ወላይታ ሶዶ እና ድሬዳዋ ከተሞች ለሚተገበረው የ“ብቃት” ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል፡፡

የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥለሁን በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በፕሮጀክቱ በ11 ከተሞች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆኑ ከ70 ሺህ በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሠራል ብለዋል።

“ብቃት” የተሰኘው ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመተግበር የተቀረጸ ነው፡፡

ለፕሮጀክቱ ትግበራ 65 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት መመደቡ ተጠቁሟል፡፡

ሥራ አጥነት በከተሞች 70 በመቶ መድረሱ እና 30 ነጥብ 4 በመቶ የሚሸፍኑት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 የሚሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡

ይህ ፕሮጀክት በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች በዘላቂነት ሥራ እንዲያገኙ የሚተገበር ሲሆን÷ 60 በመቶ ያህል ሥራ አጥ ሴቶችን የማቀፍ ትኩረት እንዳለው አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡

በነጻነት ሰለሞን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.