Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ችግሮችን በንግግር መፍታት ይገባል – አቶ ርስቱ ይርዳው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ችግሮችን በንግግር መፍታት ይገባል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከደቡብ እና ከሲዳማ ክልል ለተውጣጡ የካቢኔ አባላት በዘላቂና ሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ ፕሮግራም ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በሀዋሳ እየተካሔደ ነው፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በምክክር መድረኩ እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት አመታት በተከሰተ የሰላም እጦት ብዙ ዋጋ ከፍለናል ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ችግሮችን በንግግር መፍታት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በግጭት አፈታት ላይ  ባሉ ማህበረሰባዊ እሴቶች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው የሰላምን ጥቅም የምናውቀው ሰላም ሲታጣ  መሆኑን በመጥቀስ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማግኘት የምንችለው ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የተቀረጸው የሰላም ፖሊሲ ብቻውን ትርጉም የለውም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ ማስፈጸሚያ ፕሮግራም መቅረጽ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የውይይቱ አብይ አጀንዳ ዘላቂ ሰላም እንዴት መገንባት እንደሚቻል ማመላከት ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው መናገራቸውን ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.