ከሰሊጥና አኩሪ ዐተር ሰብሎች ከ11 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል – የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የምርት ዘመን ከሰሊጥ እና አኩሪ ዐተር ሰብሎች ከ11 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ከ450 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን፥ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ላይ ደርሷል።
ከ330 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በአኩሪ ዐተር ሰብል ተሸፍኗል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
በግብርና ሚኒስቴር የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች ልማትና ድህረ ምርት ዴስክ ሀላፊ አቶ ፍስሀ ቶሎሳ፥ ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለቱ ሰብሎች በክላስተር የለማ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ሰብሎች በማልማት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም በክልሉ 347 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በሰሊጥ፣ ከ248 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በአኩሪ ዐተር መሸፈኑን ነው በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ እንየ አሰፋ የተናገሩት።
ከዚህም ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ባለሙያዋ፥ እስካሁንም ከ44 ሺህ ሄክታር በላይ የሰሊጥ ሰብል መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን