Fana: At a Speed of Life!

የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው በዛሬው ዕለት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው ባለፈው ሳምንት ባህር ዳር በተካሄደው የጣና ፎረም ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው የሳይንስ ሙዚየምን የጎበኙ ሲሆን ÷በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ላይም ተሳትፈዋል፡፡

በተጨማሪም ከልዑካቸው እና ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ጋር በመሆን በባህር ዳር የሚገኙ የልማት ተቋማትን ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሶማሌ ክልል በመጓዝም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ በተለያዩ የክልሉ ከተሞችም ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ ከርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ጋር በመሆን ከሸበሌ ዞንና የጎዴይ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ጋርም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የመጨረሻ ጉብኝታቸውን ጎዴይ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ረፋድ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.