ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤትን መርቀው ከፈቱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤትን መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቡራዩ ከተማ የተገነባውን የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት መርቀው ከፍተዋል።
የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቱ ልዩ ችሎታ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተሰጥኦዋቸውን የሚያወጡበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በርካታ ባለተሰጥኦዎች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡
እነዚህ ባለተሰጥኦዎች ያላቸውን ተሰጥኦ አበልጽገው ወደ ምርትና አገልግሎት ለመቀየር ሲያስቡ የትምህርት ቆይታቸውን ማጠናቀቅ ግድ ይላቸዋል፣ አሊያም ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠርላቸው ባክነው ይቀራሉ።
ዛሬ የተመረቀው የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤትም ይህንን ችግር የሚቀርፍ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ትምህርት ቤቱ ባለተሰጥኦዎችን በመለየት ከመደበኛ መማር ማስተማር ሳይለዩ ልዩ ተሰጥኦዋቸውን የሚያበለጽጉበት ነው ተብሏል፡፡
ህንጻው ማደሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ህንጻ ፣ የህክምና ማዕከል፣ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራ ፣ ቤተ መጽሐፍ እና ወርክ ሾፖች ያሉት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ሁሉንም አገልግሎቶች የሚሰጡ ግብዓቶች የተሟሉለት መሆኑ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ዓለማችን በቴክኖሎጂ መጥቃለች፤ሀገራችን ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂ ከሚያስገኛቸው እንደ ኢኮኖሚ ያሉ ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን፣ በዘርፉ የላቀ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራቷ ግድ ነው ብለዋል።
ባለ ተሰጥኦ ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎታቸውን እያዳበሩ፣ ሀገራቸውን በቴክኖሎጂ ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ እንዲያሰልፉ፣ እንደ ቡራዩ የተሰጥዖ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት ያሉ የተሰጥዖ ማዕከላትን ማብዛት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ በልዩ ልዩ መንገድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአካባቢው ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአልአዛር ታደለ