በ150 ሚሊየን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የሞጆ ደረቅ ወደብ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መመሪያ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲከናወን የሥራ መመሪያ ተሰጠ፡፡
የፕሮጀክቱ የሥራ ኃላፊዎች የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚህም ከ4 መቶ ሜትሪክ ቶን በላይ አፈር ቆረጣ፣ ከ30 ሺህ ቶን በላይ የአፈር ሙሌት፣ ለኮንቴነሮች ማራገፊያ የሚሆን የመሬት ንጣፍ ለመሥራት የሚያገለግል ኮንክሪት የማምረት ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡
በተያዘው ፍጥነት መቀጠል ከተቻለ በቀጣይ ወራት የፕሮጀክት አፈፃፀሙን ከ50 በመቶ በላይ ማድረስ እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በሰጡት የሥራ መመሪያ÷ ፕሮጀክቱ እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥ የሚኖረው ከፍተኛ ጠቀሜታን ከግምት በማስገባት በተጀመረው ፍጥነት ልክ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
የሲሚንቶ አቅርቦትን በተመለከተ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ይሠራል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡