Fana: At a Speed of Life!

በሥራና ሠራተኛ አገናኝነት ሰበብ የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ኤጀንሲዎች መኖራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝነት ሰበብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ጥናት አመላከተ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በከተማዋ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ለማረም ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱ እንዳመለካተው÷ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/11 ከሚያዘው ውጭ ሠራተኞችን በወር ለ30 ቀናት በቀን ለ24 ሰዓታት አስገድደው የሚያሠሩ ኤጀንሲዎች አሉ፡፡

ኤጀንሲዎች ከድርጅቶች ጋር ተዋውለው የሚያገኙት ገንዘብ ከፍተኛ ቢሆንም ለሠራተኛው የሚደርሰው ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ኤጀንሲዎች መሰረታዊ የሥራ አልባሳትን ሳያቀርቡ ሠራተኞች ዓመቱን መሉ በአንድ የደንብ ልብስ ብቻ እንዲሠሩ ማድረጋቸውን ያነሳው ጥናቱ፥ በዚህም ለማህበራዊ እና የጤና እክል ብሎም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የተዳረጉ ሠራተኞች መኖራቸውን አሳይቷል፡፡

በቢሮው የሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ሰብሀዲን ሱልጣን እንደገለፁት÷ ሠራተኛን በተለያዩ ተቋማት እያዘዋወሩ እንዲሠራ ማስገደድ፣ የመንግሥትን ግብር እና ለጡረታ ዋስትና በሚል ከሠራተኛው የተቆረጠውን ገንዘብ ገቢ አለማድረግ የጥናቱ ግኝቶች ናቸው።

በሠነድ ፍተሻ እና ሠራተኞችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንዲሁም በአካል ኤጀንሲዎቹ ባሉበት በመሄድ በተሠራው ጥናት÷ አድራሻቸው የማይታወቅ 30፣ ከደረጃ በታች የሚሠሩ 35፣ አስገዳጅ ተቀማጭ የዋስትና ገንዘብ የሌላቸው 22፣ ፈቃድ ያላደሱ 45፣ ሰነድ የሌላቸው ደግሞ 8 ኤጀንሲዎች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

ፈቃድ ሳይኖራቸው እና ሳያድሱ በሥራና ሠራተኛ አገናኝነት እየሠሩ የሚገኙ ኤጀንሲዎች በአምስት ቀናት ውስጥ ወደ ቢሮው በመምጣት የማያመለክቱ ከሆነ ቢሮው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተመላክቷል፡፡

በሀገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ፈቃድ ወስደው ከሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች መካከል ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው የሚሠሩት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውንም ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡

በሞሊቶ ኤልያስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.