በግልገል በለስ ከተማ “ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንበግልገል በለስ ከተማ “ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ 12ኛው የ”ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በፓናል ውይይቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን፣ ም/ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ እንዲሁም የክልሉ ምክትል አፈ ጉባዔ አለምነሽ ይባስን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
”ልማት በተግባር ስለ ኢትዮጵያ”በሚል ርዕስ እየተካሄደ የሚገኘውን የፓናል ውይይት÷ አቶ አሻድሊ ሃሰን፣ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እና ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ እየመሩት ነው።
ውይይቱም በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
ከፓናል ውይይቱ ቀደም ብሎ በተከፈተው የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ÷ ከ1950ዎቹና 60ዎቹ ጀምሮ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሁነቶች፣ በታሪክ አንጓዎች የተከሰቱ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈሉ መስዋዕትነቶችና ከኢትዮጵያ የልማት ጉዞዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሀገራዊ ክንውኖችን የሚያሳዩ ምስሎች ለዕይታ ቀርበዋል።
አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለጹት÷ የፓናል ውይይቱ በመተከል ዞን መደረጉ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተናዎች እያለፈች የመሄዷ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የነበሩ እንቅስቃሴዎች በትብብር በተሠሩ ሥራዎች መመከት በመቻሉ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቁመዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በስፋት በመጠቀም የልማት ጉዞዋን ማስቀጠል የምርጫ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሃብት 45 ሺህ ሜጋዋት ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል ጠቁመው÷ በዚህ ሥራም ጎረቤት ሀገራትን መጥቀምና ምሳሌ መሆን ይቻላል ነው ያሉት፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊነትና ማንነት የፀና መሆኑን ታሪክ እንደሚመሰክር አስገንዝበው÷ የሀገርን ልማት ለማስቀጠል የተፈጥሮ ሃብቷን ማበልፀግ እና ማልማት ብቸኛው ዕድል መሆኑን በአጽኦት ገልጸዋል፡፡
በሜሮን ሙሉጌታ