9ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) 9ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አስታውቋል።
በሽልማቱ የሚካተቱት አምራች ድርጅቶች፣ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ መለኪያዎች ተዘጋጅተው ለውድድሩ እንደ መወዳደሪያነት መቅረባቸውን እና በተቋማቱ የመስክ ምልከታ በማድረግ ዝርዝር ግምገማ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በጥራት ስራ አመራር የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማትና ድርጅቶችን መሸለምና እውቅና መስጠት እንዲሁም ጥራት የአያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም መለኪያ እንዲሆን የጥራትን ጽንሰ ሀሳብ በህብረተሰቡ ዘንድ ማስረጽ የድርጅቱ አላማ ነው ተብሏል።
በተለያዩ መንገዶች ጥሪ ከተደረገላቸው ድርጅቶች እና ተቋማት ውስጥ 45 የሚሆኑ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን 40 የሚሆኑት ድርጅቶች እስከ ውድድሩ መጨረሻ መድረሳቸው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።