ሕዝቡ ከአሸባሪው ህወሓት የቆርጦ ቀጥል ሴራ እንዲጠነቀቅ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሸባሪው ህወሓት የቆርጦ ቀጥል ሴራ እንዲጠነቀቅና በዓላማና በአቋም ከሠራዊቱ ጋር የጀመረውን ቅንጅት እንዲያጠናክር የመከላከያ ሠራዊት ጥሪ አቀረበ።
አሸባሪው ህወሓት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በትር መቋቋም ሲያቅተው የመከላከያ ሠራዊቱን ስም ማጥፋቱን እንደተያያዘው ተገልጿል፡፡
የሐሰት ፊልሞችን እያቀናበረ የውሸት ክሶችን መፈብረክ ቀጥሏል ነው የተባለው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሰላም ካስከበረላቸው ሕዝቦች የተሰጡት የምስክር ወረቀቶች እንደሚረጋግጡት÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተላበሰው ዕሴት ሕዝባዊ መሆኑን ነው፡፡
ይህም እንኳን በሀገሩ እና በሕዝቡ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮው በተግባር ተመስክሯ ብሏል መከላከያ ሠራዊት፡፡
የሽብር ቡድኑ ህወሓትና ጋሻ ጃግሬዎቹ ተቋሙን ለማፍረስ ሞክረዋል፤ ጥቅምት 24 ሌሊት በክህደት ወግተው ሊያጠፉት ተፍጨርጭዋል፤ ደጋግመው ጦር ቢመዙበትም በተቃራኒው ሽንፈት አከናነባቸው ይላል መከላከያ ሠራዊት፡፡
ይህ ሁሉ ሙከራ የከሸፈበት ሽብርተኛው ህወሓት በመጨረሻም ወደ ቆርጦ ቀጥል አመሉ መግባቱን ነው መከላከያ ሠራዊት የገለጸው፡፡
ሽብርተኛው ህወሓት አንዳንድ መከላከያ ሠራዊት አባላት በተለያየ ጊዜ ለተለያየ ዓላማ የተናገሩትን ቆርጦ እየቀጠለ የሠራዊቱን ስም በማጥፋት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በግንዘቤ እጥረትም ሆነ የጠላት መጠቀሚያ በመሆን ከዕሴቱ ውጭ የሆኑ መልክቶችን የሚያስተላልፉ አባላቱን በከፍተኛ የሥነ ምግባር ጥሰት እንደሚቀጣ ተገልጿል።
ይህን የሚያደርገውም ራሱን እያረመና እያበቃ የመሄድ ነባር ሥርዓት ስላለው እና የተልዕኮው ዋና ግብ ሕዝብን ከጉዳት መጠበቅ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
ስለሆነም ሕዝባችን ከህወሓት የቆርጦ ቀጥል ሴራ እንዲጠነቀቅና በዓላማና በአቋም ከሠራዊቱ ጋር የጀመረውን ቅንጅት እንዲያጠናክር ሲል የመከላከያ ሠራዊት ጥሪውን አቅርቧል፡፡