አፍሪካውያን ተመራማሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ተመራማሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡
የአፍሪካን የተፈጥሮ ሐብቶች በመጠቀም አረንጓዴና የአየር ንብረቷ የተመቸ አኅጉር መፍጠር ቀላልና ዘላቂ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
በኬንያ መዲና ናይሮቢ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ተመራማሪዎቹ በአፍሪካ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ቀውስ በተቻለ መጠን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም የተፈጥሮ ሐብትን በአግባቡ መጠቀምና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትን የሚያበረታታ የልማት ሞዴሎች መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው የአፍሪካ ደን ፎረም (ኤ ኤፍ ኤፍ) ዋና ጸሐፊ እና የፎረሙ ሰብሳቢ የሆኑት ጎድዊን ኮዌሮ ፥ የአፍሪካ ሰፊ የደን ሐብት የምግብ፣ የውሃ፣ የኃይልና የመድኃኒት ፍላጎቶችን ከማሟላት ባለፈ በካርቦን ልቀትና ክምችት መጠን ለመቀነስ የሚጫወቱት ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በግብፅ ሊካሄድ ከታቀደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ጉባዔ 27ኛው የፓርቲዎች ኮንፈረንስ (ኮፕ27) ስብሰባ ቀደም ብሎ የተጠራው የናይሮቢው ፎረም ከፍተኛ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተመራማሪዎችንና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነው፡፡
በዚህ ፎረም የአፍሪካን የአረንጓዴ ሽግግር ለማፋጠን ደኖች እና ሌሎች ሥነ-ምኅዳሮች ባላቸው ሚና ላይ ተመራማሪዎቹ እና የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት ውይይት እንደሚያደርጉ መገለጹን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡
የኬንያ የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጆሹዋ ኪፕሎንጌ ቼቦይዎ እንዳሉት ፥ የአየር ንብረት ምላሽንና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳደግ ደኖችና ንጹህ ውሃን ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም መገንባት አለብን፡፡
የደን ሽፋንን ማስፋትና በገጠር የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ታዳሽ የኃይል ምንጮችን እንዲጠቀሙ ማገዝ ፤ የአፍሪካ ሀገራት ከአካባቢ ብክለት ነጻ ግብን ለማሳካት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ እንደድርቅና ከፍተኛ ሙቀት መሰል አደጋዎችን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።
የአፍሪካ ደን ፎረም ከፍተኛ የፕሮግራም ባለሙያ ዶሪስ ሙታ በበኩላቸው ፥ ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ የአኅጉሪቱ የአየር ንብረት ምላሽ ስትራቴጂዎችን ማላመድ አረንጓዴ እና ሁሉን አሳታፊ ለውጥን ያመጣል ብለዋል።
በግብፅ የሚካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ጉባዔ ፥ የአፍሪካ ሀገራት አኅጉሪቱ በአየር ንብረት ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተፈጥሮ ሐብት ያለውን ወሳኝ ሚና እንዲያሳድጉ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።