በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ፍተሻ 8ሺህ ዶላርና ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሰሜን ማዘጋጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 8 ሺህ ዶላር እና ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ተያዙ፡፡
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለማወክ በህቡዕ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመረጃ ስምሪት ያረጋገጡት የጸጥታና የደኅንነት አካላት በሚጠረጠሩ አካባቢዎችና ግለሰቦች ቤት የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ እያደረጉ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ አቶ ገ/እግዚአብሔር አብርሃ በተባለ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በተደረገ ፍተሻም በሕገ ወጥ መንገድ የተቀመጠ 8 ሺህ ዶላር እንዲሁም 1 ቺኮፍ መሳሪያ ከ46 ጥይት እና 2 መጋዘን ጋር ፤ 1ኮልት ሽጉጥ ከ96 ጥይት ጋር ተይዟል፡፡
ግለሰቡ ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር ትስስር እንዳለው መጠርጠሩንና ማስረጃዎች መገኘታቸውም የተጠቆመ ሲሆን ÷በአሸባሪ ቡድኖች የግንኙነት መረቦች ላይ በሚደረጉ ክትትሎች መነሻነትም ሰንሰለታቸውን በመበጣጠስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በጸጥታና በደኅንነት አካላት የሚደረጉ ተጨማሪ ስምሪቶችም ተጠናክረው መቀጠላቸዉ ተመላከቷል፡፡
ኅብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት የሚያሳየው ተሳትፎ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል፡፡