Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጨንቻ ወረዳ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጋሞ ዞን ጨንቻ ወረዳ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎበኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በጋሞ ዞን የጨንቻ ወረዳ የአካባቢው አኗኗርና ባህል መለያ ከመሆን ባሻገር፣ በኅብረ ቀለማት ቅንብር እና በሸማኔ ጥበብ የኢትዮጵያን ብዝኃነት የሚገልጹ የሸማ እና የጥበበ ዕድ ውጤቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአነስተኛ ሥፍራ ውጤታማ በሆነ የመሬት አጠቃቀም የጨንቻ መለያ የሆነውን አፕል እና አትክልት የሚያመርቱ፣ እንዲሁም ከብት እርባታን የሚከውኑ ቤተሰቦችን መጎብኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አንድ የእምነት ተቋምም ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ በተጨማሪ ከብት እርባታ ላይ ተሠማርቶ የአካባቢውን ነዋሪዎች የወተትና የወተት ተዋጽዖ ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡

የእምነት ተቋማት ከሃይማኖታዊ ተግባራት ጎን ለጎን የማኅበረሰብን የዕለት ኑሮ የሚደግፉ ሥራዎችን መከወናቸው በፈጣሪም በሰውም ዘንድ የሚያስመሰግን አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወረዳው ጨንቻ ከተማ በሽመና ስራ በህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ያሉ ወጣቶችን ስራ ተመልክተዋል።

ወጣቶቹ ከዚህ ቀደም በአካባቢው በባህላዊ መንገድ ይሰራ የነበረን የሽመና ስራ ዘመናዊ መሳሪያዎች በመታገዝ እያዘመኑ ያሉ ናቸው።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጨንቻ ከተማ የተቀናጀ የግብርና ስራንም ተመልክተዋል።

በከተማውበአነስተኛ መሬት አፕልን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን እያለሙና እንሰሳት እያረቡ ያሉ አንድ ግለሰብን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

ይህ አይነቱ ስራ በሁሉም አካባቢዎች እንዲሰፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሀይማኖት ተቋማት በልማት ስራ ያላቸው ተሳትፎ ማሳያ የሆነ የጋሞ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ማህበረሰብ አቀፍ ስራንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመልክተዋል።

የጋሞ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በጨንቻና አካባቢው የአፕል ዝርያን ያስተዋወቀች ናት።

ቤተክርስቲያኒቱ በአካባቢው የተሻሻሉ የላም ዝርያዎችን ለህብረተሰቡ ታቀርባለች።

በአልዓዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.