Fana: At a Speed of Life!

በአጣዬ በነበረው ግጭት ከወደሙ ቤቶች መካከል በመጀመሪያው ዙር የተገነቡ 45 ቤቶች ለነዋሪዎች ተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ በተደጋጋሚ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወድመው ከነበሩ 320 ቤቶች መካከል በ27 ሚሊየን ብር የተገነቡ 45 ቤቶች ለነዋሪዎች ተላለፉ፡፡

የአጣዬ ከተማ የከተማና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አክሊሉ ገዜ እንደገለጹት÷ ዛሬ ለነዋሪዎች ከተላለፉት በተጨማሪ በይፋት ማኅበር 10 ቤቶች፣ በአልማና በኢክነስ 10 ቤቶች እና በሸዋ ሰማ የልማት ማኅበር 15 ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡

የእነዚህ 35 ቤቶች ግንባታ በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ ለነዋሪቹ እንደሚተላለፍ መናገራቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

ከ200 በላይ ቤቶች ያልተገነቡ መኖራቸውን ጠቁመው አጋርና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አሳልፍ ደርቤ በበኩላቸው÷ በተመሳሳይ 49 መጋዘኖች፣ 1 የገበያ ማዕከል እና 420 ኮንቲነሮች በመገንባት የከተማዋን እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የመኖሪያ ቤቶችን የተረከቡት የህብረተሰብ ክፍሎች ቤታቸው ተመልሶ ተገንብቶ ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹን ለነዋሪዎቹ በማስተላለፍ ሥነ ስርዓቱ ላይ÷ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ የሺጥላ እና የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድን ጨምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የአጣዬ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.