2ኛው ሀገር አቀፍ የአነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአነስተኛና ቀላል የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽንና ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራልና የክልል የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የክልልና ከተማ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ መድረኩ ተቋሙ ከምስራቅ አፍሪካ አነስተኛና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አካባቢያዊ ማስተባበሪያ ቦን ኢንተርናሽናል የግጭት ጥናቶች ማዕከል ከተባለ የጀርመን ድርጅት እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
ሀገራችን የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዓት ለማስያዝ በግንባር ቀደምትነት በ1996 ዓ.ም የናይሮቢ ዲክላሬሽን ፈርማለች፤ ቀጥላም በ2012 ዓ.ም የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን አውጥታለች ብለዋል፡፡
ይህንኑ ተከትሎም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአዋጁ መሠረት የተሰጠውን ስልጣን በመጠቀም የአዋጁን ማስተግበሪያ መመሪያ አዘጋጅቶ በማጽደቅ ወደ ተግባር ገብቷል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ዛሬ የተዘጋጀው መድረክ ለአዋጁና ለመመሪያው ተፈፃሚነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡
አነስተኛና ቀላል መሣሪያዎች ከጎረቤት ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዳለና ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራጩ ለተለያዩ ግጭቶች ማባባሻ በመሆናቸው ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚሁ መሠረት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ነው የገለፁት፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ሳይገባ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ታጥቆ መስራት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩም የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች የኢትዮጵያ መንግስት እና ተቋሙ በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ላይ እየሠራ ያለውን ተግባር ማድነቃቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡