ኮርፖሬሽኑ በ486 ሚሊየን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ስራ ከሚጀምሩ 3 ኩባንያዎች ጋር ተፈራረመ
አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ486 ሚሊየን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ስራ ከሚጀምሩ ሶስት ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የውል ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እና የኩባንያዎቹ ዋና ስራ አስኪያጆች ተፈራርመዋል።
ኩባንያዎቹ በሐዋሳ፣ አዳማ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመግባት ስራ የሚጀምሩ ሲሆን÷ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን እንደሚፈጥሩም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አክሊሉ ታደሰ÷ ኩባንያዎቹ የተሰማሩበት መስክ ሀገሪቱ ለጨርቃ ጨርቅ እና የህክምና መሳሪያዎች ምርት ጥሬ ዕቃ ግዢ የምታውለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ በማስቀረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች ዝግጅት ላላቸው ወጣቶች የሚፈጥሩት የስራ ዕድል ለእውቀት ሽግግሩ የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ይበልጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለስራቸው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡