ገለልተኛ የኢኮኖሚ መማክርት ጉባዔ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ጉባዔ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡
መንግስትን በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እንዲያማክር የተቋቋመው መማክርት ጉባዔው ከብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ባደረገው የጋራ ስብሰባ ያከናወናቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ከመንግሥት የሚቀርብለትን የምክረ ሐሳብ ጥያቄዎች እንዲሁም ራሱ በሚያደርጋቸው ጥናቶች መሰረት ጠቃሚ ሐሳቦችን ለመስጠት የሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን ጉባዔው አስታውቋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላቱ ጥናቱ በመንግሥት የተዘጋጀውን የሦስት ዓመት የማገገሚያ ዕቅድ ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
መማክርቱ ጠቃሚ ሐሳቦችን በማመንጨት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ማሳሰባቸውን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉባዔውን መንግስት በበጀት እንደሚደግፈው የተገለጸ ሲሆን፥ ለመማክርቱ ተጠሪ የሆነ ሴክሬተሪያት እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
ጉባዔው የእርስበርስ ግጭትና የኢኮኖሚ መዘዞች በሚል ርዕስ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ያካሄደውን ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡