የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛምቢያ ሉሳካ አቅራቢያ 27 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጨውን ዘገባ አጣራለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛምቢያ መዲና ሉሳካ አቅራቢያ 27 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጨውን ዘገባ እንደሚያጣራ አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በደረሰው አደጋ የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
እንዲሁም በህገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ሲሉ ህይወታቸውን ማጣታቸው መዘገቡን ገልፆ አደጋውን ለማጣራት ሚኒስቴሩ ባለሙያዎችን ወደ አካባቢው በማሰማራት ከዛምቢያ መንግስት ጋር እንደሚሰራም አረጋግጧል፡፡
ቀደም ሲል በተመሳሳይ ሁኔታ ማላዊ ውስጥ ህይወታቸው ያለፉ ወገኖችን ሁኔታ ለመመርመር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተመራ ቡድን በአገሪቱ እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡
ይህ አደጋ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወገኖቻችን ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መከላከል እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላትና ዜጎች የተቀናጀ ጥረት አሁንም አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያሳይም ገልጿል፡፡