በአማራ ክልል የኮሮናቫይርስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለ7 ሺህ 650 ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማረሚያ ቤቶች የኮሮናቫይርስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለ7 ሺህ 650 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን አስታወቀ።
የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንደገለፀው ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች ውስጥ 7 ሺህ 527 የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 123 የሚሆኑት ደግሞ ሴት ታራሚዎች ናቸው ተብሏል።
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ከሰው መግደል ውጭ በሆኑ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በመታረም ላይ የሚገኙ፣ የሚያጠቡ እናቶች ፣ በአመክሮ የመፈቻ ጊዜያቸው እስከ አንድ ዓመት የቀራቸው እና ቀላል ወንጀል ፈጽመው እስከ አንድ ዓመት የቀራቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የሌሎች አገራት ዜጎች ሆነው ከሰው መግደል ውጭ በሆኑ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በመታረም ላይ የሚገኙ ሶስት ታራሚዎችም ይገኙበታል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ እና የተለያዩ ክልሎች ጠቅላይ አቃቤ ህጎች በማረሚያ ቤቶች አካባቢዎች ሊኖር በሚችለው መተፋፈግ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ለመከላከል በሺዎች ለሚቆጠሩ የህግ ታራሚዎች ይቅርታ በማድረግ እና ጉዳያቸው በመታየት ላይ የሚገኙትን ደግሞ ክሳቸውን በማቋረጥ መፍታታቸው ይታወሳል።
በናትናኤል ጥጋቡ