Fana: At a Speed of Life!

የመሬት ወረራ ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ተደራራቢ ክስ ተመስርቶ ክርክር እየተካሔደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዐቃቤ ሕግ ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በመመሳጠር በአርሶ አደርነት ስም የመሬት ወረራ ፈጽመዋል ባላቸው ዘጠኝ ግለሰቦች ላይ በከባድ የሙስና ወንጀል 4 ተደራራቢ ክሶችን መስርቶ ክርክሩን እያካሔደ ነው፡፡

ሦስት የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ ዘጠኝ ግለሰቦች ላይ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በመመሳጠር በአርሶ አደር ስም የባለይዞታነት መብት በመፍጠርና ይህን ይዞታ ለ3ኛ ወገን ሕገ ወጥ በሆነ ሽያጭ በማስተላለፍ ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ጥቅም ማካበታቸው ተመላክቷል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ጋር በጋራ ያከናወነውን ምርመራ መሰረት አድርጎ÷ በከባድ የሙስና ወንጀል አራት ተደራራቢ ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎት መስርቶ ክርክሩን እያካሔደ ነው፡፡

ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል ድንጋጌ የዋስትና መብትን የሚያስከለክል በመሆኑ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ተከሳሾች ክሱ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ጥፋተኞችም አይደለንም ሲሉ ክደው በመከራከራቸው÷ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የወንጀሉን መፈጸም የሚያስረዱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ለችሎቱ በማሰማት ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.