ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ የስኳር አቅርቦት እጥረት እንደሚቀረፍ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ የስኳር አቅርቦት እጥረት እንደሚቀረፍ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ስራ አቁመው የነበሩ የስኳር ፋብሪካዎች ምርት ማምረት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ የስኳር አቅርቦት እጥረት ይቀረፋል የተባለው፡፡
በጸጥታ ችግር እና በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት የስኳር ፋብሪካዎች ማምረት በማቆማቸው እና በውጪ ምንዛሪ እጥረት ከውጪ ተገዝቶ ባለመግባቱ ላለፉት ጥቂት ወራት የስኳር እጥረት መከሰቱ ይታወሳል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው ርብርብም በአሁኑ ሰዓት ወንጅ፣ ኦሞ 2 እና 3 እንዲሁም ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ማመረት ጀምረዋል ተብሏል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ ለሚከበረው የገና በዓል ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ሌሎችም ስኳር የሚጠቀሙ ተቋማት የኮታቸውን 25 በመቶ ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
በሀገር ውስጥ ከሚመረተው በተጨማሪ ከውጪ የሚገባውም ግዥ የተፈጸመ ሲሆን ከመጭው ጥር ወር ጀምሮ የስርጭቱን ኮታ መቶ በመቶ ማዳረስ እንደሚቻልና አሁን የተስተዋለው የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ይቀረፋል መባሉን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡