Fana: At a Speed of Life!

ለገናና ጥምቀት በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳይከሰት እየተቆጣጠርን ነው – የደቡብ እና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልሎች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪዎቹ የገና እና ጥምቀት በዓላት አስፈላጊ የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረባቸውን የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ንግድ ቢሮዎች አስታወቁ፡፡

የደቡብ ክልልን ግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሽፈራው ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠር ቢሮው ከታችኛው መዋቅር ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው፡፡

በዚህ መሰረትም ለበዓላቱ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሊትር የምግብ ዘይት በሁሉም የክልሉ መዋቅሮች ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡

በተመሳይ 86 ሺህ ኩንታል ስኳር በክልሉ በሁሉም ዞኖች በሚገኙ ዩኒየኖች በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሰራጨ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ከበዓላት ውጭ በዋጋ መጨመር ህብረተሰቡ እንዳይጎዳም የሰንበት ገበያዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተቋቁመው ወደስራ መግባታቸውንም አስረድተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው፥ በክልሉ ለመጪዎቹ በዓላት የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው፡፡

ለዚህም በሁሉም ዞኖች የገበያ ስርዓቱን የሚቆጣጠር ግብረ ሃይል መቋቋሙን ጠቁመው፥ ኮሚቴው በእስካሁኑ ስራ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ለገናና እና ጥምቀት በዓላት 900 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለህብረተሰቡ እየተሰራጨ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከስኳር ጋር በተያያዘ በክልሉ እጥረት መኖሩን የገለጹት ሃላፊው፥ ለበዓላቱ የቀረበው ከዚህ በፊት ይቀርብ ከነበረው 25 በመቶው ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሎቹ የእርድ እንስሳትን እና ግብርና ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የእሁድ ገበያዎች፣ ባዛሮች፣ የሸማች ማህበራት እና ሌሎች መንገዶች መመቻቸታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዓላቱን ምክንያት በማድረግ ነጋዴዎች ከፀረ-ውድድና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ፣ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በአንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እና የዜጎችን ጤንነት የሚጎድ ምርቶችን ከማቅረብ እንዲቆጠቡ ቢሮዎቹ አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.