በላሊበላ የተከበረው የገና በዓል በሰላም ተጠናቋል–ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በላሊበላ በድምቀት የተከበረው የገና በዓል ያለምንም ፀጥታ ችግር መጠናቀቁን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ኮማንደር እንግዳው ሆዴነው እንደገለፁት÷ በበአሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእምነት አባቶች፣ በሃገሪቱ ከአራቱም አቅጣጫዎች የመጡ እንግዶችን ጨምሮ የውጭ ሃገር ዜጎችና አምባሳደሮች በድምቀት አክብረው ውለዋል።
በዓሉ በሰላም ለማክበር አስቀድሞ በተካሄደ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ የቅድመ ዝግጅ ስራ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ማክበር መቻሉን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአሁኑ ሰዓት እንግዶች በዓሉን አክብረው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ኮማንደሩ ምስጋና አቅርበዋል።