በጋምቤላ ክልል ከነገ ጀምሮ የስራ ሰዓት ለውጥ ይደረጋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ከነገ ጀምሮ ለውጥ እንደሚደረግ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፒተር ሆው እንደገለጹት÷ በክልሉ የሙቀቱ መጨመር ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት የሚቆይ የስራ ሰዓት ለውጥ ይደረጋል።
በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል የመደበኛው የስራ ሰዓት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ተኩል የነበረው ከ1 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ተኩል እንደሚሆን አስታውቀዋል።
እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ9 ሰዓት እስከ 11 ተኩል የነበረው ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል እንዲሆን መወሰኑን ጠቅሰዋል፡፡
የስራ ሰዓት ለውጡ በማጃንግ ዞን የመንገሽና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር መግለጻቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በለውጡ መሰረት ሰራተኞች በተጠቀሰው የስራ ስዓት መስሪያ ቤታቸው በመገኘት የተለመደ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ሀላፊው አስገንዝበዋል።