መንግስት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራ ላይ በትኩረት እየሠራ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የውጭ ጉይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሳምንቱ በተከናወኑ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የኳታር፣ የፓኪስታን፣ የቻይና እና ሌሎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የሰላም ሁኔታ በመጠቀም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንዲሁም የሁለትዮሽ ንግድና የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምሩ የተቀናጀ የማግባባት ስራ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ አማካኝነት ውይይቶች መካሄዳቸው ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ5ኛው የተመድ የአዳጊ ሀገራት ጉባኤ የነቃ ተሳትፎ እንደነበራቸው በማብራሪያው አንስተዋል፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን÷ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብደል ፈታሕ አል ቡርሃን እና ከየመን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕን አብዱልማሊክ ሰኢድ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ከኳታሩ ኤሚር ሼክ ተሚም ኢብን ሀማድ አልታኒ ጋር በኢትዮጵያና ኳታር ሁለትዮሽ ግንኙነትና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ለኳታር ኢንቨስትመንቶች ብዙ ዕድሎች እንዳሉ መገለጹ እንዲሁም በኢትዮጵያ ባለው የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም እና ዕድል ዙሪያ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል።
የኳታር ባለሀብቶች ልዑክ በቅርቡ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱም ተመላክቷል፡፡
በኮንስትራክሽን በግብርናና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ለቅድመ ኢንቨስትመንት ጥናት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎታቸውን ገልጸዋልም ነው ያሉት።
ከ71 በላይ አባላት ያሉት የፓኪስታን ልዑክ በአዲስ አበባ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያነሱት።
እንዲሁም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፥ በዚህ ወቅትም ከአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄይሁን ባይራሞቭ ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንም አስረድተዋል።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለመምከር የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና የስራ ጉብኝት ማድረጉንም አስታወሰዋል።
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኳታር ከሀገሪቱ የንግድ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ከኳታር መንግስት ባለስልጣናት ጋር መክረዋል፡፡
በካናዳ፣ በእንግሊዝና አሜሪካ ውጤታማ የንግድ መድረኮች በተከታታይ መከናወናቸውንም ነው አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ዘልቆ ከቆየው ግጭት በኃላ መንግስት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም የድህረ ግጭት የምጣኔ ሀብት ማነቃቂያ ስልት በመንደፍ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል፡፡