በአዲስ አበባ መናና ወንዝ የአንድ ሰው ሕይወት አልፎ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መናና ወንዝ ውስጥ የ35 ዓመት ግለሰብ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የኮሚሽኑ ዋናተኞች አስከሬኑን አውጥተው ለፖሊስ አስረክበዋል፡፡
በሌላ በኩል በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ፊጋ መብራት አካባቢ ከረፋዱ 4 ከ06 ሐመር ሆቴል ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 3:15 መፍጀቱን የተናገሩ አቶ ንጋቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጠቁመዋል።
እንዲሁም ዛሬ ከቀኑ 8:37 ሰዓት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ 72 ኖክ በሚባል ነዳጅ መቅጃ ጣቢያ ውስጥ ኮሮላ የቤት አውቶሞቢል ነዳጅ ቀድቶ ከነዳጅ ማደያው በመውጣት ላይ ሳለ በእሳት ተያይዞ ሙሉ በሙሉ ወድሟል።
በእሳት አደጋው አንድ የነደጅ ማደያ ሰራተኛ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ ወደ ህክምና መላኩን አስረድተዋል።
የእሳት አጀጋው ወደነደጃ ማደያው ተዛምቶ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፥ ነዳጅ ለመቅዳት ወደ ነዳጅ ጣቢያ የሚገቡና ቀድተው የሚወጡ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮሐንስ ደርበው