በደቡብ ክልል ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ከ246 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ከ246 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበስቧል።
መጽሐፉን የማስተዋወቅ እና የመሸጥ መርሐ ግብር በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ጢያ ከተማ ጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን ለማልማት እንደሚውል አስረድተዋል፡፡
የታሰበውን ገንዘብ በመሰብሰብ በአጭር ጊዜ ስራውን ለማስጀመር ግብ ተይዟል ማለታቸውን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ገሩማ÷ የመስኅብ ስፍራው በተያዘለት ዕቅድ ልክ እንዲለማ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎች የመደመር ትውልድ መጽሐፍን በመግዛት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመስኅብ ስፍራው ሙዚየም፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የማህበራዊ እና ባህላዊ አስተዳደርን አጉልቶ የሚሳይ አንፊ ቴአትር እንዲሁም የአካባቢውን ባህል ብሎም የግብርና ውጤቶችን የሚያሳዩ የተለያዩ ተክሎችን ያካተተ ልማት እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡