ሰሞኑን በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮቸ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀናቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሣምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሀገራት በግል በተደረጉ የጎዳና ላይ ውድድሮቸ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡
በቻይና ውሃን ከተማ በተደረገ የጎዳና ላይ ውድድር አትሌት ትዕግስት ታደሰ 2ኛ ሆና ስታጠናቀቅ÷ በዥንግ ካይ የወንዶች ማራቶን አትሌት ታፈረ አዲሱ፣ ገለታ ስንታዬሁ እና ወርቁ ድረሴ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
እንዲሁም በቻይና ዩዌይንግ በተካሄደ ውድድር በወንዶች አትሌት ፈቃዱ የሽጥላ ቀዳሚ በመሆን ሲጨርስ÷ በሴቶች ኮሎሌ መካሹ እና ሳምራዊት ነጋ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በኔዘርላንድስ ሮተርዳም በተካሄደ የማራቶን ውድድር በወንዶች አትሌት ዳዊት ወልዴ 4ኛ፣ ጫላ ረጋሳ 5ኛ፣ አስማረ ባዘዘው 7ኛ እና አበበ ነገዎ 8ኛ ደረጃን ሲይዙ÷ በሴቶች አትሌት ቲኪ ገላና 6ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
በፖላንድ በተካሄደው የጎዳና ላይ ውድድርም አትሌት ሙሉ ቱሉ 2ኛ በመሆን ርቀቱን ሲያጠናቅቅ÷ በፖላንድ ፖንዛን በተካሄደ ውድድር ደግሞ አትሌት ሃብታሙ ገ/ስላሴ፣ ሰለሞን በሪሁ እና ህዝቅያስ ታምራት ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡
በሴቶቹ አትሌት አንችዓለም ሃይማኖት ቀዳሚ ስትሆን ልቅና አምባው 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቋን ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በጣልያን ቶሪኖ እና ጀኖዋ ከተሞች በተካሄዱ ውድድሮች በሴቶች አስመራወርቅ ኦልቀባ ስታሸነፍ÷ በወንዶች ኃይሉ ኢቲቻ 2ኛ እንዲሁም ፈቃዱ መርጋ 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡
በሌላ የውድድር መርሐ ግብር በፈረንሳይ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን አትሌት ኩባ ዓለሙ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ርቀቱን ስታጠናቅቅ÷ በአሜሪካ ቦስተን ማራቶን በተመሳሳይ በሴቶች አትሌት መቅደስ አበበ አሸንፋለች፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች በተደረገ ውድድር በወንዶቸ አትሌት ጣሃ ጉደቶ ሲያሸንፍ በዚሁ ርቀት በሴቶች እማዋይሽ ቢሆነኝ ርቀቱን በበላይነት አጠናቃለች፡፡