ቤንያሚን ኔታንያሁና ተፎካካሪያቸው ቤኒ ጋንዝ ጥምር መንግስት ለመመስረት ስምምነት ፈረሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁና ተፎካካሪያቸው ቤኒ ጋንዝ በአስቸኳይ ጥምር መንግስት ለመመስረት ስምምነት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሯል።
በስምምነቱ መሰረትም ቤንያሚን ኔታንያሁና ተፎካካሪያቸው ቤኒ ጋንዝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስፍራን በተራ የሚይዙ መሆነቡም ታውቋል።
በዚህም ቤንያሚን ኔታንያሁ በመጀመሪያ ዙር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን የሚይዙ ሲሆን፥ ለ18 ወራት ማለትም ለ1 ዓመት ከ6 ወር እስራኤልን የሚመሩ ይሆናል።
በመቀጠልም ተፎካካሪያቸው የቀድሞ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስፍራውን ተረክበው ለተመሳሳይ 18 ወራት ማለትም ለ1 ዓመት ከ6 ወር እስራኤልን ለመምራት ከስምምነት ደርሰዋል።
የአስቸኳይ ጥምር መንግስት ምስረታውም በትናንትናው እለት ምሽት በእየሩሳሌም በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መፈረሙም ታውቋል።
በሁለቱ ተፎካካሪዎች መካከል ጥምር መንግስት ለመመስረት የተደረሰው ስምምነት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶስት ምርጫዎችን ላረገችው እስራኤል የፖለቲካ መረጋጋትን የሚያመጣ መሆኑም ታውቋል።
አስቸኳይ ጥምር መንግስቱን ለማቋቋም ያስፈለገውም ዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በእስራኤል እያደረሰ ያለውንብ ጉዳት ለመከላከል መሆኑም ታውቋል።
የስምምነት ፊርማውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፥ “አሁን የተቋቋመው አስቸኳይ የጥምር መንግስት የእስራኤል ዜጎችን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ” ብለዋል።
ቤኒ ጋንዝ በበኩላቸው፥ “አራተኛ ዙር ምርጫ በእስራኤል እንዳይካሄድ አድግርገናል፤ ዴሞክራሲን እንጠብቃለን፤ እንዲሁም ኮሮናቫርየስን በመዋጋት ለእስራኤል ዜጊች አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን” ብለዋል።
እንደ እስራኤል ጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆፐነ እስካሁን በእስራኤል በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ13 ሺህ 700 የበለጠ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የ177 ሰዎች ህይወት አልፏል።
ምንጭ፦ bbc.com