ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚችል የማምረት አቅም አላት -የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚችል የማምረት አቅም እንዳላት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡
ፅህፈት ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው ፅሁፍ÷ ኅብረትን፣ ልማትን እና አንድነትን ገንዘብ ካደረግን ኢትዮጵያ ማምረት ትችላለች ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በቂ መሬት፣ በቂ ውኃ፣ አምራች ወጣት፣ ምርትን መደገፍ የሚችል ኢነርጂ፤ የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሁም አስቻይ የሆነ የማምረቻ አውድ ያላት ሀገር መሆኗን አንስቷል፡፡
በማዕድን ዘርፍ ግብዓት መሆን የሚችሉ ማዕድናት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ የጠቆመው ፅህፈት ቤቱ÷ በማዕድን ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ለኢንዱስትሪው ማደግ ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንዳላቸው አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በግብርና ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ ለኢንዱስትሪው ግብዐት መሆን ይችላሉ ያለው ፅህፈት ቤቱ በዚህም የምርት ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል አረጋግጧል፡፡