ከውጪ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የበለጠ መስራት ይገባል – የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር የሚገቡ የኢንዱስትሪ ነክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የበለጠ መስራት ይገባል ሲሉ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ሃገራዊ ንቅናቄ አካል የሆነ የጥቃቅን አምራች ኢንዱስትሪዎችን የፈጠራ ውጤቶችን ለማበረታታት እና የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ ያለመ አውደ-ርዕይ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እያደረገች ባለው ግስጋሴ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር መስራቱ የበለጠ የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአውደ-ርዕዩ ላይ የተሳተፉ የጥቃቅንና አነስተኛ የኢንዱስትሪ ውጤት አምራቾችም ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር መሰል መድረኮች አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱላቸው ገልጸዋል፡፡
በአውደ-ርዕዩ ላይ ከክልሉ የተውጣጡ 120 የሚሆኑ ኢንተሪፕራይዞች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
በነገኦ ብዙነህ