ባለፉት 9 ወራት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል – የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ÷ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን በአርባምንጭ ከተማ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀሙን በገመገመበት ወቅት ገልጿል፡፡
በአፈፃፀሙ ላይ በአገልግሎት ዘርፍ ለ1 ሚሊየን ዜጎች የስራ አድል እንደተፈጠረ የተገለጸ ሲሆን÷ በግብርና ለ962 ሺህ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፉ ለ493 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ተጠቁሟል፡፡
በስራ እድል ፈጠራው የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልፀዋል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በውጭ ሀገራት ስምሪትም ለ59 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ነው የተገለፀው፡፡
ሚኒስቴሩ ከውጭ ሀገራት ስምሪት ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሰራ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን÷ በማንዋል የነበሩ የውጭ ሀገር ስምሪት ስራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዜጎችን ሲያስተጎጉሉ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ ተችሏልም ተብሏል፡፡
ባለፉት ወራት በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች በመደበኛ እና አጫጭር ስልጠናዎች ሙያተኞችን የማፍራት ስራ ተከናውኗልም ነው የተባለው፡፡
በግምገማው በስራ አድል ፈጠራ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እና በውጭ ሀገራት ስምሪት የተገኙ ስኬቶችና መሻሻል ያሉባቸው ጉዳዮች መለየታቸውም ተነስቷል፡፡
በኤፍሬም ምትኩ